፲፪
፩ በዚያም ዘመን ንጉሡ ሄሮድስ መከራ ያጸናባቸው ዘንድ ከቤተ ክርስቲያኑ በአንዳንዶቹ ላይ እጁን ጫነባቸው።
፪ የዮሐንስንም ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ ገደለው።
፫ አይሁድንም ደስ እንዳሰኛቸው አይቶ ጨምሮ ጴጥሮስን ደግሞ ያዘው። የቂጣ በዓልም ወራት ነበረ።
፬ በያዘውም ጊዜ ወደ ወኅኒ አገባው ከፋሲካም በኋላ ወደ ሕዝብ ያወጣው ዘንድ አስቦ እያንዳንዱ አራት ወታደሮች ሆነው እንዲጠብቁት ለአራት ጭፍራ ክፍል አሳልፎ ሰጠው።
፭ ጴጥሮስም በወኅኒ ይጠበቅ ነበር፤ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ስለ እርሱ ወደ እግዚአብሔር ጸሎት አጥብቆ ይደረግ ነበር።
፮ ሄሮድስም ሊያወጣው ባሰበ ጊዜ፥ በዚያች ሌሊት ጴጥሮስ በሁለት ሰንሰለት ታስሮ ከሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ ጠባቂዎችም በደጁ ፊት ሆነው ወኅኒውን ይጠብቁ ነበር።
፯ እነሆም፥ የጌታ መልአክ ቀረበ በቤትም ውስጥ ብርሃን በራ፤ ጴጥሮስንም ጎድኑን መትቶ አነቃውና። ፈጥነህ ተነሣ አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጁ ወደቁ።
፰ መልአኩም። ታጠቅና ጫማህን አግባ አለው፥ እንዲሁም አደረገ።
፱ ልብስህንም ልበስና ተከተለኝ አለው። ወጥቶም ተከተለው፤ ራእይንም የሚያይ ይመስለው ነበር እንጂ በመልአኩ የሚደረገው ነገር እውነት እንደ ሆነ አላወቀም።
፲ የመጀመሪያውንና የሁለተኛውንም ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደሚያወጣው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ፤ እርሱም አውቆ ተከፈተላቸው፤ ወጥተውም አንዲት ስላች አለፉ ወዲያውም መልአኩ ከእርሱ ተለየ።
፲፩ ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ። ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ አለ።
፲፪ ባስተዋለም ጊዜ እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደ ተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት መጣ።
፲፫ ጴጥሮስም የደጁን መዝጊያ ባንኳኳ ጊዜ ሮዴ የሚሉአት አንዲት ገረድ ትሰማ ዘንድ ቀረበች፤
፲፬ የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ የተነሣ ደጁን አልከፈተችም፥ ነገር ግን ወደ ውስጥ ሮጣ ጴጥሮስ በደጅ ፊት ቆሞ እንዳለ አወራች።
፲፭ እነርሱም። አብደሻል አሉአት። እርስዋ ግን እንዲሁ እንደ ሆነ ታስረግጥ ነበር። እነርሱም። መልአኩ ነው አሉ።
፲፮ ጴጥሮስ ግን ማንኳኳቱን አዘወተረ፤ ከፍተውም አዩትና ተገረሙ።
፲፯ ግን ዝም እንዲሉ በእጁ ጠቅሶ ጌታ ከወኅኒ እንዴት እንዳወጣው ተረከላቸውና። ይህን ለያዕቆብና ለወንድሞች ንገሩ አላቸው። ወጥቶም ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ።
፲፰ በነጋም ጊዜ። ጴጥሮስን ምን አግኝቶት ይሆን? ብለው በጭፍሮች ዘንድ ብዙ ሁከት ሆነ።
፲፱ ሄሮድስም አስፈልጎ ባጣው ጊዜ ጠባቂዎችን መረመረ ይገድሉአቸውም ዘንድ አዘዘ፤ ከይሁዳም ወደ ቂሣርያ ወርዶ በዚያ ተቀመጠ።
፳ ከጢሮስና ከሲዶና ሰዎችም ጋር ተጣልቶ ነበር፤ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ መጡ፥ የንጉሥንም ቢትወደድ ብላስጦስን እሺ አሰኝተው ዕርቅ ለመኑ፥ አገራቸው ከንጉሥ አገር ምግብ ያገኝ ነበረና።
፳፩ በተቀጠረ ቀንም ሄሮድስ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በዙፋን ተቀመጠ እነርሱንም ተናገራቸው፤
፳፪ ሕዝቡም። የእግዚአብሔር ድምፅ ነው የሰውም አይደለም ብለው ጮኹ።
፳፫ ለእግዚአብሔርም ክብር ስላልሰጠ ያን ጊዜ የጌታ መልአክ መታው በትልም ተበልቶ ሞተ።
፳፬ የእግዚአብሔር ቃል ግን ያድግና ይበዛ ነበር።
፳፭ በርናባስና ሳውልም አገልግሎታቸውን ፈጽመው ከኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስንም ከእነርሱ ጋር ይዘውት መጡ።